የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው፤ ክብርን ይጐናጸፋል፤ በዙፋኑ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል የሰላም ምክር ይኖራል።’
የልዑል አምላክ ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤
ለስሜ ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።
እግዚአብሔር ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” አለው።
“እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት፤ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሎ፣ እግዚአብሔር ምሏል፤ እርሱ ሐሳቡን አይለውጥም።
ሕይወትን ለመነህ፤ ረዥም ዘመናትንም እስከ ዘላለም ሰጠኸው።
በአቀዳጀኸው ድል ክብሩ ታላቅ ሆነ፤ ክብርንና ግርማን አጐናጸፍኸው።
በዚያም ቀን፣ የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ አሕዛብ እርሱን ይፈልጋሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል።
የቤተ ሰቡ ክብር፣ ልጅና የልጅ ልጅ፣ እንዲሁም ከማሰሮ ጀምሮ እስከ ጋን ድረስ ያለ የቤት ዕቃ ሁሉ በርሱ ላይ ይንጠለጠላል።
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
የጦረኞች ጫማ ሁሉ፣ በደም የተለወሰ ልብስም ሁሉ፣ ለእሳት ይዳረጋል፤ ይማገዳልም።
ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል።
ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።
“እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር።
በርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም ያለ ሥጋት ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል።
“ ‘በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት ጻድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ፤ በምድሪቱም ፍትሕንና ጽድቅን ያደርጋል።
በእግዚአብሔር ኀይል፣ በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ታላቅነት፣ ጸንቶ ይቆማል፤ መንጋውንም ይጠብቃል። በዚያ ጊዜ ኀያልነቱ እስከ ምድር ዳርቻ ስለሚደርስ፣ ተደላድለው ይኖራሉ።
እርሱም፣ “እነዚህ ሁለቱ የምድርን ሁሉ ጌታ ለማገልገል የተቀቡ ናቸው” አለኝ።
“የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ፤ የሚፈጽሙትም የርሱ እጆች ናቸው። ከዚያም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እኔን ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
ወርቁንና ብሩን ወስደህ አክሊል ሥራ፤ በኢዮሴዴቅ ልጅ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ራስ ላይም አድርገው፤
እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም አለን።
በቈላስይስ ለሚኖሩ፣ በክርስቶስ ለሆኑ ቅዱሳንና ታማኝ ወንድሞች፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
እንግዲህ የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፤ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ።
ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው። እርሱም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኗል።
እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋራ በርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋራ በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።