በዚያ ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤
ዳዊት ግን እያለቀሰ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፤ ራሱን ተከናንቦ፣ ባዶ እግሩን ነበር፤ ዐብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ሽቅብ ይወጣ ነበር።
የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማዪቱ ውስጥ ተነሥቶ ወጣ፤ ከከተማዪቱም በስተምሥራቅ ካለው ተራራ በላይ ቆም አለ።
የባሕር ዓሦች፣ የሰማይ ወፎች፣ የምድር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጡር ሁሉ፣ እንዲሁም በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ፣ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮች ይገለባበጣሉ፤ ገደሎች ይናዳሉ፤
እኔም የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ ድምፁ እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ነበር፤ ምድሪቱም ከክብሩ የተነሣ ታበራ ነበር።
ቆመ፤ ምድርን አንቀጠቀጠ፤ ተመለከተ፤ ሕዝቦችን አብረከረከ፤ የዘላለም ተራሮች ተፈረካከሱ፤ የጥንት ኰረብቶችም ፈራረሱ፤ መንገዱ ዘላለማዊ ነው።
ምድር ሁሉ ከጌባዕ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሪሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።
ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።
በዚያ ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።
“ታላቅ ተራራ ሆይ፤ አንተ ምንድን ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎች፣ ‘ሞገስ ይሁንለት! ሞገስ ይሁንለት!’ ብለው እየጮኹ፣ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል።”
እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል።