እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”።
ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፤ እንደ አካሄዱም ይከፍለዋል።
ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።
አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርሁት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።”
አንተም፣ “ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም” ብትል፣ ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን? ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?
ልባቸው ዐመፅን ያውጠነጥናልና፤ ከንፈራቸውም ሸፍጥ ያወራል።
ሞኝን ወይም የትኛውንም ዐላፊ አግዳሚ የሚቀጥር፣ ፍላጻውን በነሲብ እየወረወረ ወገኖቹን እንደሚያቈስል ቀስተኛ ነው።
እኔም በልቤ፣ “ለማንኛውም ድርጊት፣ ለማንኛውም ተግባር ጊዜ ስላለው፣ አምላክ ጻድቁንና ኀጢአተኛውን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል” ብዬ አሰብሁ።
“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ፤ የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
ዕቅድህ ታላቅ፣ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ዐይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።
መሞት የሚገባት ኀጢአት የሠራችው ነፍስ ናት። ልጅ በአባቱ ኀጢአት አይቀጣም፤ አባትም በልጁ ኀጢአት አይቀጣም። ጻድቁ የጽድቁን ፍሬ ያገኛል፤ ኀጢአተኛውም የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።
“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ፤ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
በአሕዛብ መካከል በተንኋቸው፤ እነርሱም በየአገሩ ተበታተኑ፤ እንደ ጠባያቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው።
የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ከመላእክት ጋራ ይመጣል፤ ለእያንዳንዱም ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይከፍለዋል።
እንግዲያስ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለህ እምነት በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የተጠበቀ ይሁን፤ ትክክል ነው ብሎ በተቀበለው ነገር ራሱን የማይኰንን የተባረከ ሰው ነው።
የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል።
ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
እንግዲህ የርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እያንዳንዱም ሰው በሥጋው ለሠራው በጎ ወይም ክፉ ሥራ ተገቢውን ዋጋ ይቀበላል።
አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጕዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል።
ልጆቿንም በሞት እቀጣቸዋለሁ። ከዚያም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ ልብንና ሐሳብን የምመረምር መሆኔን ይረዳሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ።
ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው።
“እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ።