እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ታላቅ ንጉሥ ነው።
ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ “አሜን! አሜን!” ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለብሰሃል።
እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፣ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁና።
እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም።
በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።
ሕዝቦችን ከእኛ በታች አደረገ፤ መንግሥታትንም ከእግራችን ሥር አስገዛልን።
እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴውም ብዙ ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል ነህና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ያልህ ነህ።
“እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጓልና።”
አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወቅኋችሁምን? ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ! ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”
ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ “በሕያውነቴ እምላለሁ”። በተራሮች መካከል ያለውን የታቦር ተራራ የሚመስል፣ ባሕርም አጠገብ ያለውን የቀርሜሎስ ተራራ የሚመስል አንድ የሚመጣ አለ።
ሞዓብ ትጠፋለች፤ ከተሞቿም ይወረራሉ፤ ምርጥ ወጣቶቿም ወደ መታረድ ይወርዳሉ፤” ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ፤
የሰማይ አምላክ የሚያደርገው ሁሉ ትክክል፣ መንገዶቹም ሁሉ ጽድቅ ስለ ሆኑ፣ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር እርሱን አወድሰዋለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ አከብረዋለሁም፤ እርሱም በትዕቢት የሚመላለሱትን ማዋረድ ይችላል።
“ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ በየስፍራውም ሁሉ ለስሜ ዕጣንና ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“በመንጋው ውስጥ ተቀባይነት ያለው ተባዕት በግ ኖሮት ይህንኑ ሊሰጥ ተስሎ ሳለ፣ በማታለል ነውር ያለበትን እንስሳ ለጌታ የሚሠዋ ርጉም ይሁን፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ ሊፈራ የሚገባ ነውና” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤
በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ ስለ ሆነ አያስደንግጡህ።