እግዚአብሔር በቅዱሳን ጉባኤ መካከል በጣም የሚፈራ፣ በዙሪያውም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የሚከበር ነው።
እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር፣ በላይ በዙፋኑ የተቀመጠ ማን ነው?
እናንተ ኀያላን፣ ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ።
በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።
ጌታ ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋራ የሚወዳደር ሥራ የለም።
እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋራ ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋራ ታነጻጽሩታላችሁ?
ቅዱሱ፣ “ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።
እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን? እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።
የሕዝቦች ሁሉ ንጉሥ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ ማነው? ክብር ይገባሃልና። ከምድር ጠቢባን ሁሉ፣ ከመንግሥቶቻቸውም ሁሉ መካከል፣ እንደ አንተ ያለ የለም።
ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር፦ “ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣ እከበራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ።
ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።
መላዪቱን ቤተ ክርስቲያንና ይህን የሰሙትን ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ያዛቸው።