አምላክ ሆይ፤ መንገድህ ቅዱስ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?
ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤ ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ።
የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
ስለዚህ በመቅደስ ውስጥ አየሁህ፤ ኀይልህንና ክብርህንም ተመለከትሁ።
መዘምራን ከፊት፣ መሣሪያ የሚጫወቱ ከኋላ ሆነው ሲሄዱ፣ ከበሮ የሚመቱ ቈነጃጅትም በመካከላቸው ነበሩ።
አምላክ ሆይ፤ ጽድቅህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤ አንተ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤ አምላክ ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣ መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር።
ጌታ ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋራ የሚወዳደር ሥራ የለም።
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ?
እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋራ ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋራ ታነጻጽሩታላችሁ?
ቅዱሱ፣ “ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።
“ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋራ እኩል ታደርጉኛላችሁ? እንመሳሰልስ ዘንድ ከማን ጋራ ታነጻጽሩኛላችሁ?
የእነርሱ መጠጊያ ዐለት እንደ እኛ መጠጊያ ዐለት አይደለምና፤ ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን አይክዱም።