ለስሙ ክብር ዘምሩ፤ ውዳሴውንም አድምቁ።
ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ። “ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል።
ስለ እግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ማን ሊናገር ይችላል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ተናግሮ ይጨርሳል?
እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ።
ከጥንት ጀምሮ ከነበሩት ሰማያት በላይ ለወጣው፣ በኀያል ድምፁ ለሚያስገመግመው ዘምሩ።
ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ።
አዳኛችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤ ስለ ስምህ ክብር ብለህ ርዳን፤ ስለ ስምህ ስትል፣ ታደገን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በል።
ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ።
ሰማያት ሆይ፤ እልል በሉ፤ ምድር ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ተራሮች ሆይ፤ በደስታ ዘምሩ! እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል፤ ለተቸገሩትም ይራራልና።
እርስ በርሳቸው በመቀባበልም፣ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለች” ይሉ ነበር።
ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”