ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።
ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤ አንተም የሁሉ ገዥ ነህ፤ ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣ ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው።
ሰው ባያስተውለውም፣ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል፤
ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፤ እንደ አካሄዱም ይከፍለዋል።
ሁሉን ቻይ አምላክ ከአእምሯችን በላይ ነው፤ በኀይልና በፍርድ ታላቅ ነው፣ ጽድቁም ብዙ ነው፤ ማንንም አይጨቍንም።
የኀይል ነገር ከተነሣ፣ እርሱ ኀያል ነው! የፍትሕም ነገር ከተነሣ፣ መጥሪያ ሊሰጠው የሚችል ማን ነው?
የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤
እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው።
ጌታ ሆይ፤ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ ለቍጣ የዘገየህ፣ ምሕረትህና ታማኝነትህ የበዛ።
ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ፤ ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ ወሰን የለውም።
አንተም፣ “ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም” ብትል፣ ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን? ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?
ዕቅድህ ታላቅ፣ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ዐይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።
“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ፤ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
ይሁን እንጂ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”
ንጉሡ ያለቅሳል፤ መስፍኑ ተስፋ መቍረጥን ይከናነባል፤ የምድሪቱም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች። የእጃቸውን እከፍላቸዋለሁ፤ ራሳቸው ባወጡት መስፈርት መሠረት እፈርድባቸዋለሁ። “ ‘በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”
አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው።
ምንም እንኳ በርሱ ላይ ያመፅን ብንሆን፣ ጌታ አምላካችን ይቅር ባይና መሓሪ ነው።
የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ከመላእክት ጋራ ይመጣል፤ ለእያንዳንዱም ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይከፍለዋል።
እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”።
የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል።
ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እያንዳንዱም ሰው በሥጋው ለሠራው በጎ ወይም ክፉ ሥራ ተገቢውን ዋጋ ይቀበላል።
ምክንያቱም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።
በደለኛውም የእጁን ያገኛል፤ አድልዎም የለም።
ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደየሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ።
“እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ።