ዝቅተኞችና ከፍተኞች፣ ባለጠጎችና ድኾች ይህን በአንድነት ስሙ።
ሁሉም የእጁ ሥራ ስለ ሆኑ፣ እርሱ ለገዦች አያደላም፤ ባለጠጋውንም ከድኻው አብልጦ አይመለከትም።
ከተናቀ ወገን መወለድ ከንቱ፣ ከከበረውም መወለድ ሐሰት ነው። በሚዛን ቢመዘኑ፣ የሰው ልጆች ሁሉ በአንድነት ከነፋስ የቀለሉ ናቸው።
ባለጠጋና ድኻ የሚጋሩት ነገር፣ እግዚአብሔር የሁላቸውም ፈጣሪ መሆኑ ነው።
እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ኑ አድምጡም፤ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አስተውሉ። ምድርና በውስጧ ያለ ሁሉ፣ ዓለምና ከርሷ የሚበቅል ሁሉ ይስማ!
እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤ ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤ ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣ ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።