እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሳነዋልን? እርሱ ልብ የሰወረውን የሚረዳ ነውና።
እግዚአብሔር ሲነሣ ምን አደርጋለሁ? ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ?
እርሱ መንገዴን አያይምን? ርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
መልካምም ይሁን ክፉ፣ ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ ማንኛውንም ሥራ አምላክ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።
“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ፤ የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
እኔ እንዳላየው፣ በስውር ቦታ ሊሸሸግ የሚችል አለን?” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን” ይላል እግዚአብሔር።
ይህም በወንጌል እንደማስተምረው እግዚአብሔር በሰው ልብ የተሰወረውን በክርስቶስ በኩል በሚፈርድበት ዕለት ግልጽ ይሆናል።
ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
ልጆቿንም በሞት እቀጣቸዋለሁ። ከዚያም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ ልብንና ሐሳብን የምመረምር መሆኔን ይረዳሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ።