እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው። ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው፤ ሕዝቦችም ከምድሩ ይጠፋሉ።
መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እግዚአብሔርን አመስግኚ፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽን አወድሺ።
“እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ እልል በሉ፤ በደስታም ዘምሩ፤ በመካከላችሁ ያለው የእስራኤል ቅዱስ ታላቅ ነውና።”
አንተ ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር፤ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትነግር፣ ድምፅህን በኀይል ከፍ አድርገህ ጩኽ። ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፣ “እነሆ፤ አምላካችሁ!” በል።
በተራሮች ላይ የቆሙ፣ የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች፣ ሰላምን የሚናገሩ፣ መልካም ዜና የሚያበሥሩ፣ ድነትን የሚያውጁ፣ ጽዮንንም፣ “አምላክሽ ነግሧል!” የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።
ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።
“በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
“በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ። “እርሱ ለዘላለም የሚኖር፣ ሕያው አምላክ ነውና፣ መንግሥቱ አይጠፋም፤ ለግዛቱም መጨረሻ የለውም።
ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።
“ከዚያም እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር፣ በቅዱሱ ተራራዬ በጽዮን እንደምኖር ታውቃላችሁ፤ ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲያ ባዕዳን አይወርሯትም።
ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤ “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና የርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤ እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”