በጠራሁህ ቀን መልስ ሰጠኸኝ፤ ነፍሴን በማደፋፈርም ብርቱ አደረግኸኝ።
በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም በፊቱ ከጆሮው ደረሰ።
እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤ ልቤ ሐሤት አደረገ፤ በዝማሬም አመሰግነዋለሁ።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታትን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።
እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም።
ነፍሴ አንተን የሙጥኝ ብላለች፤ ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች።
እነሆ፣ አምላክ ድነቴ ነው፤ እታመናለሁ፣ ደግሞም አልፈራም፤ ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ድነቴም ሆኗል።”
እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
ገና ሳይጣሩ እመልስላቸዋለሁ፤ ተናግረው ሳይጨርሱ እሰማለሁ።
በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ “አትፍራ” አልኸኝ።
እንደ ገናም፣ ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም።
እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና” አለኝ። እየተናገረኝም ሳለ፣ በረታሁና፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አበርትተኸኛልና ተናገር” አልሁት።
በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፤ በስሙም ይመላለሳሉ” ይላል እግዚአብሔር።
በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤
በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ።
ኀይልን በሚሰጠኝ በርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ።
ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ሰዎቹ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ነፍሳቸው ተመራ ሊወግሩት ስለ ተመካከሩ ዳዊት በጣም ተጨነቀ፤ ነገር ግን ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር በረታ።