ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።
ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና።
ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ።
ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል።
ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣ በቃልህ ደስ አለኝ።
ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣ እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤ ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤ ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል።
ደግሞም አገልጋይህ በርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤ እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው።
ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!
ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤
ፍሬዬ ከንጹሕ ወርቅ ይበልጣል፤ ስጦታዬም ከነጠረ ብር።
ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው።