ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል።
በመንገዱም ሁሉ እንድንሄድ፣ ለአባቶቻችን የሰጣቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ደንቦች እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ።
ክፉ ሰው በልቡ ምኞት ይኵራራል፤ ስግብግቡን ይባርካል፤ እግዚአብሔርንም ይዳፈራል።
ከዐመፀኞች ጋራ፣ በክፉ ሥራ እንዳልተባበር፣ ልቤን ወደ ክፉ አታዘንብል፤ ከድግሳቸውም አልቋደስ።
አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺሕ፣ የመቶ፣ የዐምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው።
ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው ዘወትር ይፈሩኝ ዘንድ፣ አንድ ልብ አንድም ሐሳብ እሰጣቸዋለሁ።
ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ሕዝቤ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህንም ለመስማት ከፊትህ ይቀመጣሉ፤ ነገር ግን አይፈጽሙትም። በከንፈራቸው ብዙ ፍቅርን ይገልጣሉ፤ ልባቸው ያረፈው ግን ተገቢ ባልሆነ ጥቅም ላይ ነው።
“በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን ለሚገነባ፣ ከጠላት እጅ ለማምለጥ፣ ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት!
ደግሞም፣ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ” አላቸው።
ገንዘብ የሚወድዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው በኢየሱስ ላይ አፌዙበት።
ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኩሰት ወይም የሥሥት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና።
ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው።
በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል።
ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ሥሥትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው!
እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን እየተስገበገቡ በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዟችኋል። ፍርዳቸው ከጥንት ጀምሮ ዝግጁ ነው፤ መጥፊያቸውም አያንቀላፋም።