አሕዛብ ሁላችሁ፤ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ሕዝቦችም ሁሉ፤ ወድሱት፤
እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።
ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል ይበል!
ምድር ሁሉ ይሰግድልሃል፤ በዝማሬ ያመሰግኑሃል፤ ለስምህም ይዘምራሉ።” ሴላ
እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤ ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።
ጌታ ሆይ፤ አንተ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ፣ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ለስምህም ክብር ይሰጣሉ፤
እንደ ገናም፣ “አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑት፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወድሱት” ይላል።
ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና። የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ።”
እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ “መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።