ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናት።
የሰሜንን ሰማይ በሕዋው ላይ ዘረጋው፤ ምድርንም እንዲያው በባዶው ላይ አንጠለጠላት።
ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።
ምድርን በውሃ ላይ የዘረጋ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቷታልና፤ በውሆችም ላይ አጽንቷታል።
እርሱ ተናግሯልና ሆኑ፤ አዝዟልና ጸኑም።
እግዚአብሔር ነገሠ፤ ግርማንም ተጐናጸፈ፤ እግዚአብሔር ግርማን ለበሰ፤ ብርታትንም ታጠቀ፤ ዓለም እንዳትናወጥ ጸንታለች፤ ማንም አይነቀንቃትም።
በሕዝቦች መካከል፣ “እግዚአብሔር ነገሠ” በሉ፤ ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥምም፤ እርሱ ለሕዝቦች በእኩልነት ይፈርዳል።
ለባሕር ድንበርን በከለለ ጊዜ፣ ውሆችም የርሱን ትእዛዝ እንዳያልፉ፣ የምድርንም መሠረቶች ወሰን ባበጀ ጊዜ፣
ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል።
ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም።
ሰማይ እንደ ጥቅልል መጽሐፍ ተጠቅልሎ ዐለፈ፤ ተራሮችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ።
እርሱ ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤ ምስኪኑንም ከጕድፍ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ከመኳንንቱ ጋራ ያስቀምጣቸዋል፤ የክብር ዙፋንም ያወርሳቸዋል። “የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፣ ዓለምን በእነርሱ ላይ አድርጓል።