እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቷል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።
እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤ አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።
ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤ አንተም የሁሉ ገዥ ነህ፤ ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣ ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው።
እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን በሰማይ ነው። ዐይኖቹ ሰዎችን ይመለከታሉ፤ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።
አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል።
በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።
በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።
እግዚአብሔር ግን ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፤ መንበሩንም ለፍርድ አጽንቷል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ቤት የት ትሠሩልኛላችሁ? ይላል ጌታ፤ ወይስ ማረፊያ የሚሆነኝ ቦታ የት ነው?
“ ‘ውሳኔው በመልእክተኞች ተገልጿል፤ ፍርዱም በቅዱሳኑ ተነግሯል፤ ይኸውም፣ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።’
ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋራ ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል።
ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።
እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤
እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።