እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው፤ ሕዝቦችም ከምድሩ ይጠፋሉ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤ አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።
መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው። ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔር በጐርፍ ላይ ዙፋኑን ዘርግቶ ተቀምጧል፤ እግዚአብሔር በንጉሥነቱ ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ይቀመጣል።
ሕዝቦችን ከፊታቸው አባረረ፤ ምድራቸውን ርስት አድርጎ በገመድ አከፋፈላቸው፤ የእስራኤልንም ነገዶች በጠላቶቻቸው ቤት አኖረ።
አሕዛብ በቈፈሩት ጕድጓድ ገቡ፤ እግራቸውም ራሳቸው በስውር ባስቀመጡት ወጥመድ ተያዘ።
ሕዝቦችን ገሠጽህ፤ ክፉዎችንም አጠፋህ፤ ስማቸውንም እስከ ወዲያኛው ደመሰስህ።
ዓለምን በጽድቅ ይዳኛል፤ ሕዝቦችንም በፍትሕ ይገዛል።
እግዚአብሔር ነገሠ፤ ግርማንም ተጐናጸፈ፤ እግዚአብሔር ግርማን ለበሰ፤ ብርታትንም ታጠቀ፤ ዓለም እንዳትናወጥ ጸንታለች፤ ማንም አይነቀንቃትም።
“እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ የሚያድነንም እርሱ ነውና።
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ለዘላለም ትገዛለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ፣ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁት፤ ለዘላለምም የሚኖረውን ወደስሁት፤ ክብርንም ሰጠሁት። ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነው፤ መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
“በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ። “እርሱ ለዘላለም የሚኖር፣ ሕያው አምላክ ነውና፣ መንግሥቱ አይጠፋም፤ ለግዛቱም መጨረሻ የለውም።
እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያሉትን አሕዛብ እንዳጠፋቸው ሁሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችሁ እናንተም ትጠፋላችሁ።
እንግዲህ ዘላለማዊ ለሆነው፣ ለማይሞተው፣ ለማይታየውና ብቻውን አምላክ ለሆነው ንጉሥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ምስጋና ይሁን። አሜን።