ባለጠጋ ራሱን ጠቢብ አድርጎ ይቈጥር ይሆናል፤ አስተዋይ የሆነ ድኻ ግን መርምሮ ያውቀዋል።
ጠቢባን የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ ብቻ አይደሉም፤ የሚያስተውሉም ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም።
የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤ እንደማይወጣ ረዥም ግንብም ይቈጥሩታል።
አስቀድሞ ጕዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው።
ንግግሩ ጠማማ ከሆነ ሞኝ ሰው ይልቅ፣ ያለ ነውር የሚሄድ ድኻ ሰው ይሻላል።
ሀብት ለማግኘት ስትል ራስህን አታድክም፤ ሐሳብህን የመግታት ጥበብ ይኑርህ።
ራሱን እንደ ጠቢብ የሚቈጥረውን ሰው አይተሃልን? ከርሱ ይልቅ ለሞኝ ተስፋ አለው።
በማስተዋል መልስ ከሚሰጡ ከሰባት ሰዎች ይልቅ፣ ሰነፍ ራሱን ጠቢብ አድርጎ ይቈጥራል።
ሞኝን እንደ ቂልነቱ መልስለት፤ አለዚያ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል።
በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።
ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፣ በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው!
ወንድሞች ሆይ፤ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ፣ ይህን ምስጢር ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል በድንዳኔ ውስጥ ዐልፋለች።
እርስ በርሳችሁ በአንድ ሐሳብ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋራ ዐብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ።
በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።