ተግሣጽን የሚንቅ ራሱን ይንቃል፤ ዕርምትን የሚቀበል ግን ማስተዋልን ያገኛል።
ተግሣጼን ትጠላለህና፤ ቃሌንም ወደ ኋላህ ትጥላለህ።
እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ ቂሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
ተግሣጽን ነቅቶ የሚጠብቅ የሕይወትን መንገድ ያሳያል፤ ዕርምትን የማይቀበል ግን ሌሎችን ወደ ስሕተት ይመራል።
ተግሣጽን የሚንቅ ወደ ድኽነትና ኀፍረት ይሄዳል፤ ዕርምትን የሚቀበል ሁሉ ግን ይከበራል።
አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤ የሞኝ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል።
ልበ ቢስ ሰው ቂልነት ያስደስተዋል፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ይከተላል።
ሕይወት ሰጪ የሆነውን ተግሣጽ የሚሰማ፣ በጠቢባን መካከል ይኖራል።
እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን መማር ነው፤ ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።
ቂል የአባቱን ምክር ይንቃል፤ መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል።
ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣ ሞኝ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው?
የአስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይገበያል፤ የጠቢብም ጆሮ አጥብቆ ይሻታል።
ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ።
ከብዙ ተግሣጽ በኋላ ዐንገቱን የሚያደነድን ሰው፣ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።
የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣ የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል።
ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ? ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ? ራሳችሁ በሙሉ ታምሟል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኳል።
የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤ አይደብቁትምም፤ ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ፣ ወዮላቸው!
እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህ እውነትን አይመለከቱምን? አንተ መታሃቸው፤ እነርሱ ግን አልተሰማቸውም፤ አደቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን አልታረሙም፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠነከሩ በንስሓ ለመመለስም አልፈለጉም።
አንድ ሰው፣ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፣ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣
“ይህ ልጃችን እልከኛና ዐመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው” ብለው ለከተማው አለቆች ይንገሯቸው።
ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ።
ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ።
እኔ የምወድዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ።