የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤ የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል።
ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት፤ ሰይፍ በከንፈራቸው ላይ አለ፤ “ማን ሊሰማን ይችላል?” ይላሉና።
ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።
የጻድቃን ከንፈሮች ተገቢውን ነገር ያውቃሉ፤ የክፉዎች አንደበት ግን የሚያውቀው ጠማማውን ብቻ ነው።
አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል፤ ሞኝ ግን ቂልነቱን ይገልጣል።
የጠቢብ አንደበት ዕውቀትን ታወድሳለች፤ የሞኞች አንደበት ግን ቂልነትን ያፈልቃል።
የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤ ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ።
ሞኝ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቅቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል።
በችኰላ የሚናገርን ሰው ታያለህን? ከርሱ ይልቅ ሞኝ ተስፋ አለው።
በአፍህ አትፍጠን፤ በአምላክም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣ በልብህ አትቸኵል፤ አምላክ በሰማይ፣ አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤ ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን።
አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። አምላክ በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?
እናንተ የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና።
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና።