በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል።
እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር።
እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።
አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ፤ ጠላቶቼም አይዘባነኑብኝ።
ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከርሱ ዘንድ ነውና።
የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የክፉዎች ተስፋ ግን ከንቱ ሆኖ ይቀራል።
ለነገ ርግጠኛ አለኝታ ይኖርሃል፤ ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።
እስራኤል ግን በእግዚአብሔር፣ በዘላለም ድነት ይድናል፤ እናንተም ለዘላለም፣ አታፍሩም፤ አትዋረዱም።
ጌታ እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ አልዋረድም፤ ስለዚህ ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌአለሁ፤ እንደማላፍርም ዐውቃለሁ።
“አይዞሽ አትፍሪ፤ ኀፍረት አይገጥምሽም፤ ውርደት ስለማይደርስብሽ አትሸማቀቂ፤ የወጣትነት ኀፍረትሽን ትረሺዋለሽ፤ የመበለትነት ስድብሽንም ከእንግዲህ አታስታውሺውም።
ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።
ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።
ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ዝግጁ ነኝ” አላቸው።
ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።
ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
በተፈጥሮ ደካሞች ስለ ሆናችሁ፣ በሰው ቋንቋ ይህን እላለሁ፤ ብልቶቻችሁን በባርነት ለርኩሰትና እየባሰ ለሚሄድ ክፋት ታቀርቡ እንደ ነበር፣ አሁን ደግሞ ወደ ቅድስና ለሚወስደው ጽድቅ ባሪያ አድርጋችሁ አቅርቡ።
ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል።
ይህም፣ “እነሆ፤ የሚያደናቅፍ ድንጋይ፣ የሚጥልም ዐለት፣ በጽዮን አስቀምጣለሁ፤ በርሱም የሚያምን አያፍርም” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ።
በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
በዚህም ልቡ ተከፍሏል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዐላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች።
ጌታ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበልነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና።
እንግዲህ ይህን የመሰለ ተስፋ ስላለን፣ በድፍረት እንናገራለን።
የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን።
በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።
በእናንተ ላይ ያለኝን ትምክሕት ለርሱ ነግሬው ነበር፤ እናንተም አላሳፈራችሁኝም። ነገር ግን ስንነግራችሁ የነበረው ሁሉ እውነት እንደ ሆነ፣ እንደዚሁም ስለ እናንተ ለቲቶ በትምክሕት የነገርነው እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።
በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ትልቅ ነው፤ በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም።
በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል።
ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋራ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ።
ስለ እናንተ በተቀበልሁት መከራ አሁንም ደስ ይለኛል፤ ክርስቶስ ስለ አካሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበለው መከራ የጐደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ።
የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና ሥጋችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ነቀፋ ይጠበቁ።
ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን፣ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
እንግዲህ ልጆች ሆይ፤ እርሱ ሲገለጥ ድፍረት እንዲኖረን፣ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በርሱ ኑሩ።