ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረቡት እንስሳት የእህል ቍርባናቸውን ጨምሮ ድምራቸው፦ ዐሥራ ሁለት ወይፈን፣ ዐሥራ ሁለት አውራ በግ፣ ዐሥራ ሁለት አንድ ዓመት የሆናቸው ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሆነ፤ እንዲሁም ለኀጢአት መሥዋዕት የቀረቡ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎች ነበሩ።
ዕጣን የሞላባቸው ዐሥራ ሁለቱ የወርቅ ጭልፋዎችም እያንዳንዳቸው በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ዐሥር ሰቅል መዘኑ፤ በአጠቃላይ የወርቅ ጭልፋዎቹ ክብደት አንድ መቶ ሃያ ሰቅል ነበር።
ለኅብረት መሥዋዕት የቀረቡት እንስሳት ድምር ሃያ አራት በሬ፣ ስድሳ አውራ በግ፣ ስድሳ ተባዕት ፍየልና ስድሳ አንድ ዓመት የሆናቸው ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበር። እንግዲህ መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመሠዊያው መቀደስ የቀረቡ ስጦታዎች እነዚህ ናቸው።