ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤
ለአንዱ ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ለአንድ አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን አድርጎ፣ ለእያንዳንዱም ኢፍ አንድ የሂን መስፈሪያ ዘይት ዐብሮ ያቅርብ።
የአሮንም ልጆች በመሠዊያው በሚነድደው ዕንጨት ላይ ባለው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አድርገው ያቃጥሉት፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል።
እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።
ከሰባቱ የበግ ጠቦቶችም ከእያንዳንዳቸው ጋራ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።