እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፤ “ከምድራቸው የምትካፈለው ርስት፣ ከእነርሱም የምታገኘው ድርሻ የለህም፤ በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።
ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ “አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ታላቅ ዋጋህም እኔው ነኝ።”
እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ደግሞም፣ “አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ በሕያዋንም ምድር ዕድል ፈንታዬ ነህ” እላለሁ።
እግዚአብሔር የርስት ድርሻዬና ጽዋዬ ነው፤ ዕጣዬም በእጅህ ናት።
ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣ የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው።
ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።”
“ ‘ለካህናቱ ርስታቸው እኔ ብቻ ነኝ፤ በእስራኤል ምንም ዐይነት ርስት አትስጧቸው፤ እኔ ርስታቸው እሆናለሁ።
ይሁን እንጂ በመሠዊያው ላይ የሚደረገውንና በመጋረጃ ውስጥ ያለውን ማንኛውንም የክህነት አገልግሎት የምትፈጽሙት አንተና ልጆችህ ብቻ ናችሁ፤ የክህነቱን አገልግሎት ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከእናንተ በቀር ወደ መቅደሱ የሚጠጋ ቢኖር ግን ይገደል።”
አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ተቈጥረው ሃያ ሦስት ሺሕ ሆኑ፤ እነርሱም ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋራ ርስት ተካፋዮች ስላልነበሩ ዐብረዋቸው አልተቈጠሩም።
ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር ነው።
እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ሐሤት አድርጉ።
የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው፣ በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው።
ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።
ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቍርባን በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።
ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው እርሱ ራሱ ርስታቸው ነውና።
ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን ዐብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤
ሌዋውያኑ ግን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ርስታቸው ስለ ሆነ በእናንተ መካከል ድርሻ አይኖራቸውም። ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምሥራቅ ዮርዳኖስ የሰጣቸውን ርስት ቀደም አድርገው ወስደዋል።”
ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋራ ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋራ ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል።