ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብጻውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤
ስለዚህ በመቅሠፍቱ እንዳያጠፋቸው ይመለስ ዘንድ፣ እርሱ የመረጠው ሙሴ በመካከል ገብቶ፣ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፣ እንደሚያጠፋቸው ተናግሮ ነበር።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ሙሴና ሳሙኤል እንኳ በፊቴ ቢቆሙ፣ ልቤ ለዚህ ሕዝብ አይራራምና ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ!
ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።
ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብጽ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።
ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፣ ‘ድል ያደረገችው እጃችን እንጂ፣ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፣ የጠላትን መነሣሣት ሠጋሁ።”
እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ስለ ወደደ፣ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይተውም።