እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።
ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ።
ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤
ኀጢአትን ብሠራ ትመለከተኛለህ፤ መተላለፌንም ሳትቀጣ አታልፍም።
እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰለት፤ እንዲህም አለው፤
ጥበቡ ጥልቅ፣ ኀይሉም ታላቅ ነውና፤ እርሱን ተቃውሞ ያለ አንዳች ጕዳት የሄደ ማን ነው?
እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው።
የእልፍኝህን አግዳሚ በውሆች ላይ አኖርህ፤ ደመናትን ሠረገላህ አደረግህ፤ በነፋስ ክንፍ ትሄዳለህ።
ጌታችን ታላቅ ነው፤ እጅግ ኀያልም ነው፤ ለጥበቡም ወሰን የለውም።
አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፤ የሚባላ እሳት በፊቱ፣ የሚያስፈራ ዐውሎ ነፋስም በዙሪያው አለ።
እግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነው።
እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፤ “ሥራህ እንዴት ግሩም ነው! ጠላቶችህ ከኀይልህ ታላቅነት የተነሣ፣ በፊትህ ይርዳሉ።
ስለ ግብጽ የተነገረ ንግር፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጻውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በነጐድጓድ፣ በምድር መናወጥና በታላቅ ድምፅ፣ በዐውሎ ነፋስና በኀይለኛ ሞገድ፣ ፈጽሞ በሚባላም የእሳት ነበልባል ይመጣል።
እነሆ፤ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ይመጣል፤ ሠረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ ንዴቱን በቍጣ፣ ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይገልጣል።
እነሆ፤ እንደ ደመና ይንሰራፋል፤ ሠረገሎቹ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣሉ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይፈጥናሉ፤ መጥፋታችን ነውና ወዮልን!
“ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ጋራ ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
“ነፋስን ይዘራሉ፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤ አገዳው ዛላ የለውም፤ ዱቄትም አይገኝበትም፤ እህል አፍርቶ ቢገኝም፣ ባዕዳን ይበሉታል።
ልባችሁን እንጂ፣ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣ ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና።
ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁትስ ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የተነሣሁትም ለዚሁ ነበር፤ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣ የዘገየህ አምላክ፣ ምሕረትህ የበዛ፣ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ።
እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ይገለጣል፤ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔር መለከት ይነፋል፤ በደቡብም ዐውሎ ንፋስ ውስጥ ይጓዛል፤
‘እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’
ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህን አስተውሉ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤
“እነሆ፤ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሳይቀሩ፣ ዐይን ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከርሱ የተነሣ ዋይ ዋይ ይላሉ።” አዎ! ይህ ሁሉ ይሆናል። አሜን።