መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።
ክፉ ሰው ፍትሕ ለማዛባት፣ በስውር ጕቦ ይቀበላል።
ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።
እናንተ የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን ብላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ፣ በእስራኤል አምላክ የምትታመኑ፣ ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው የሚለውን አድምጡ፤
ጕቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፣ ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው!
እጅግ ሲበዛ ሆዳም ውሾች ናቸው፤ ጠገብሁን አያውቁም፤ የማያስተውሉ እረኞች ናቸው፤ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ሄዱ፤ እያንዳንዳቸውም የግል ጥቅማቸውን ፈለጉ።
እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።
ኤርምያስ ይህን ቃል በእግዚአብሔር ቤት ሲናገር፣ ካህናቱና ነቢያቱ፣ ሕዝቡም ሁሉ ሰሙ።
በእግዚአብሔር ላይ ሐሰትን ተናገሩ፤ እንዲህም አሉ፤ “እሱ ምንም አያደርግም! ክፉ ነገር አይደርስብንም፤ ሰይፍም ራብም አናይም፤
“ከትንሹ እስከ ትልቁ ሰው፣ ሁሉም ለጥቅም የሚስገበገቡ ናቸው፤ ነቢያቱም ካህናቱም ሳይቀሩ፣ ሁሉም ያጭበረብራሉ።
“ይህ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው” እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ።
ስለዚህ ሚስቶቻቸውንም ለሌሎች ወንዶች እሰጣለሁ፤ ዕርሻዎቻቸውንም ለባዕዳን እሰጣለሁ፤ ከታናሹ እስከ ታላቁ ድረስ፣ ሁሉም ተገቢ ላልሆነ ጥቅም ይስገበገባሉ፤ ነቢያትና ካህናትም እንዲሁ፤ ሁሉም ያጭበረብራሉ።
በመካከልሽ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጕቦ ይቀበላሉ፤ አንቺም ዐራጣና ከፍተኛ ወለድ በመውሰድ ከባልንጀራሽ የማይገባ ትርፍ ዘረፍሽ፤ እኔንም ረስተሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈስሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ።
“የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ራሳቸውን ብቻ ለሚከባከቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች መንጋውን ማሰማራት አልነበረባቸውምን?
መጠጣቸው ባለቀ ጊዜ እንኳ፣ ዘማዊነታቸውን አያቆሙም፤ ገዦቻቸውም ነውርን አጥብቀው ይወድዳሉ።
የሕዝቤ ኀጢአት ለመብል ሆኖላቸዋል፤ ርኩሰታቸውንም እጅግ ወደዱ።
በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፣ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ ከዚያ በኋላ እንደ ተናገራችሁት፣ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሆናል።
በሕዝቤ መካከል ያሉ፣ ‘ክፉ ነገር አያገኘንም ወይም አይደርስብንም’ የሚሉ፣ ኀጢአተኞች ሁሉ፣ በሰይፍ ይሞታሉ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣ ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤ ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣ ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።
እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ ገዥው እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ ፈራጁ ጕቦ ይቀበላል፤ ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ።
ሹሞቿ የሚያገሡ አንበሶች፣ ገዦቿ ለነገ የማይሉ፣ የምሽት ተኵላዎች ናቸው።
ነቢያቷ ትዕቢተኞች፣ አታላዮችም ናቸው፤ ካህናቷ መቅደሱን ያረክሳሉ፣ በሕግም ላይ ያምፃሉ።
“በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳት እንዳታነድዱ፣ ምነው ከእናንተ አንዱ የቤተ መቅደሱን ደጅ በዘጋ ኖሮ! እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቍርባን አልቀበልም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“ስለዚህ በመንገዴ ስላልሄዳችሁና በትምህርታችሁም አድልዎ ስላደረጋችሁ፣ በሰዎች ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አድርጌአችኋለሁ።”
ሙሴም በጣም ተቈጣ፤ እግዚአብሔርንም “ቍርባናቸውን አትቀበል፤ እኔ ከእነዚህ ሰዎች የወሰድሁት አንድ አህያ እንኳ የለም፤ አንዳቸውንም አልበደልሁም” አለ።
የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ሄዱ፤ በለዓም ዘንድ በደረሱ ጊዜም የባላቅን መልእክት ነገሩት።
‘አብርሃም አባት አለን’ በማለት አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና።
የማይሰክር፣ የማይጣላ ግን ጨዋ የሆነ፣ የማይጨቃጨቅ፣ ገንዘብንም የማይወድ ሊሆን ይገባዋል።
እነዚህን ዝም ማሠኘት ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ትክክል ባልሆነ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ ናቸው።
በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤
ወዮላቸው! በቃየን መንገድ ሄደዋል፤ ለገንዘብ ሲስገበገቡ በበለዓም ስሕተት ውስጥ ወድቀዋል፤ በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋል።
ነገር ግን ልጆቹ የአባታቸውን ፈለግ አልተከተሉም፤ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከመንገዱ ወጡ፤ ጕቦ ተቀበሉ፤ ፍርድም አጣመሙ።