“አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ፣ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤
የግብዣው ጊዜ ካለፈ በኋላ ኢዮብ ልኮ ያስመጣቸውና፣ “ምናልባት ልጆቼ ኀጢአት ሠርተው፣ እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል” በማለት ጧት በማለዳ ስለ እያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያነጻቸው ነበር፤ ኢዮብ ይህን ዘወትር ያደርግ ነበር።
በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
እነዚህ ቀኖች ካለፉ በኋላም፣ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁንና የኅብረት መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያቀርባሉ። ከዚያም እኔ እቀበላችኋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
“ወደ ተቀደሰው ስፍራ በሚገባበት ጊዜ፣ አሮን እንዲህ ያድርግ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይዞ ይምጣ፤
ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቁማቸው።
ሙሴ አሮንን፣ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተስርይላቸውም” አለው።
እርሱም እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ካህናት መጀመሪያ ስለ ራሱ ኀጢአት፣ ከዚያም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቧልና።
የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ።
ነገር ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል የሚገባው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ ከቶ አይገባም ነበር።