እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው።
“እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።
“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
እርሱም አሳን ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አሳ፣ እናንተም ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፤ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋራ ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋራ ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን፣ ይተዋችኋል።
ይሁን እንጂ የአሼራን ዐምዶች ከምድሪቱ ስላስወገድህና እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልብህን ስላዘጋጀህ፣ መልካም ነገር ተገኝቶብሃል”።
ምንም እንኳ በመቅደሱ ሥርዐት መሠረት የነጹ ሆነው ባይገኙም፣ የአባቶቻቸው አምላክ የሆነውን እግዚአብሔር አምላካቸውን ለመፈለግ ልባቸውን የሚያዘጋጁትን ሁሉ ይቅር በላቸው።”
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማገልገልም ሆነ፣ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ በመገዛት አንጻር ያደረገውን ሁሉ በፍጹም ልቡ አምላኩን በመፈለግ አከናወነ፤ ተሳካለትም።
“መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቍጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።
በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ።
ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔር ሕግ፤ ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት፤
ምስኪኖች በልተው ይጠግባሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹትም ያመሰግኑታል፤ ልባችሁም ለዘላለም ሕያው ይሁን!
እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤ ስለዚህ ኀጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።
እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
“ፊቴን ፈልጉ” ባልህ ጊዜ፤ ልቤ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን እሻለሁ አለች።
እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ።
በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።
“ጌታ ሆይ፤ አሁንስ ወደ ማን ልመልከት? ተስፋዬ በአንተ ላይ ነው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴን ስማ፤ ጸሎቴንም አድምጥ።
አምላክ ሆይ፤ ስእለቴን ሰምተሃልና፤ ስምህን የሚፈሩትንም ሰዎች ርስት ለእኔ ሰጠህ።
ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ ልባችሁ ይለምልም!
እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።
በዚያ ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፤ መንፈሴም በውስጤ ትፈልግሃለች። ፍርድህ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ፣ የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።
እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው!
እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።
እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ ከአንተ በቀር አምላክ እንዳለ ያየ ዐይን የለም፤ የሰማም ጆሮ የለም።
ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።
ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለዚህ እስከምፈርድበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፤ አሕዛብን ላከማች፣ መንግሥታትን ልሰበስብ፣ መዓቴንና ጽኑ ቍጣዬን በላያቸው ላፈስስ ወስኛለሁ። በቅናቴ ቍጣ እሳት፣ መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።
ደግሞም ከሙታን ያስነሣውንና ከሰማይ የሚመጣውን ልጁን፣ ከሚመጣውም ቍጣ የሚያድነንን ኢየሱስን እንዴት እንደምትጠባበቁ ይናገራሉ።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ።