የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤ በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤ በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ ካህናቷ ይቃትታሉ፤ ደናግሏ ክፉኛ ዐዝነዋል፤ እርሷም በምሬት ትሠቃያለች።
የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤ እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች።
መርዶ ስሙ! እነሆ፤ ከሰሜን ምድር፣ ታላቅ ሽብር እየመጣ ነው፤ የይሁዳን ከተሞች ባድማ፣ የቀበሮዎችም መናኸሪያ ያደርጋል።
“ይሁዳ ታለቅሳለች፤ ከተሞቿም ይማቅቃሉ፤ በምድር ላይ ተቀምጠው ይቈዝማሉ፤ ጩኸትም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ይሰማል።
“ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣ የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤ የይሁዳንም ከተሞች፣ ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
“ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ፤ የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም፤ ጠላቶቼ ሁሉ ጭንቀቴን ሰሙ፤ አንተ ባደረግኸውም ደስ አላቸው፤ አቤቱ የተናገርሃት ቀን ትምጣ፤ እነርሱም እንደ እኔ ይሁኑ።
ጕልማሶች ወፍጮ እንዲፈጩ ተገደዱ፤ ወንዶች ልጆች በዕንጨት ሸክም ተንገዳገዱ።
ሽማግሌዎች ከከተማዪቱ በር ሄደዋል፤ ጕልማሶች ዝማሬያቸውን አቁመዋል።
ለበኣል አማልክት ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናት እቀጣታለሁ፤ በጌጣጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤ ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤ እኔን ግን ረስታለች” ይላል እግዚአብሔር።
የዱር አራዊትን እሰድድባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤ ከብቶቻችሁን ያጠፉባችኋል፤ ቍጥራችሁ ይመነምናል፤ መንገዶቻችሁም ሰው አልባ ይሆናሉ።
ስለዚህ በእናንተ ምክንያት፣ ጽዮን እንደ ዕርሻ ትታረሳለች፣ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ የቤተ መቅደሱም ኰረብታ ዳዋ የወረሰው ጕብታ ይሆናል።