“ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤ እነርሱ ግን ከዱኝ፤ ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ፣ ምግብ ሲፈልጉ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ዐለቁ።
ታዲያ፣ ልታመልካቸው ያበጀሃቸው አማልክት ወዴት ናቸው? በመከራህ ጊዜ ሊያድኑህ የሚችሉ ከሆነ፣ ይሁዳ ሆይ፤ እስኪ ይምጡና ያድኑህ፤ የከተሞችህን ቍጥር ያህል፣ የአማልክትህም ብዛት እንዲሁ ነውና።
ወዳጆችህ ሁሉ ረስተውሃል፤ ስለ አንተም ግድ የላቸውም። ጠላት እንደሚመታ መታሁህ፤ እንደ ጨካኝም ቀጣሁህ፤ በደልህ ታላቅ፣ ኀጢአትህም ብዙ ነውና።
አንቺ ለጥፋት የተዳረግሽ ሆይ፤ ምን መሆንሽ ነው? ቀይ ቀሚስ የለበስሽው ለምንድን ነው? ለምን በወርቅ አጌጥሽ? ዐይኖችሽንስ ለምን ተኳልሽ? እንዲያው በከንቱ ተሽሞንሙነሻል፤ የተወዳጀሻቸው ንቀውሻልና፤ ነፍስሽንም ሊያጠፉ ይፈልጋሉ።
በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣ እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣ አሁን ባሪያ ሆናለች።
እንጀራ በመፈለግ፣ ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤ በሕይወት ለመኖር፣ የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤ እኔ ተዋርጃለሁና።”
በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤ እንባዋ በጕንጮቿ ላይ ይወርዳል፤ ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣ የሚያጽናናት ማንም የለም፤ ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤ ጠላቶቿም ሆነዋል።
“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እይ፤ ተመልከትም፤ በማን ላይ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ? በውኑ እናቶች ሕፃኖቻቸውን፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆች ይብሉን? ካህኑና ነቢዩስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን?
ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣ ዐይኖቻችን ደከሙ፤ ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣ ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን።
መሳፍንት በእነርሱ እጅ ተሰቀሉ፤ ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።