የዳን ነገድ በኰረብታማው ምድር ብቻ እንዲወሰን እንጂ ወደ ሜዳማው አገር እንዲወርድ አሞራውያን አልፈቀዱለትም።
ነገር ግን የዳን ዘሮች ርስታቸው አልበቃቸውም፣ ወደ ሌሼም ወጥተው አደጋ በመጣል ያዟት፤ ሰዎቹንም በሰይፍ ስለት ፈጅተው ይዞታቸው አደረጓት፤ በዚያው ሰፈሩ፤ ስሟንም ለውጠው በአባታቸው ስም ዳን አሏት።
ንፍታሌምም በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩትን አላስወጣም፤ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድሪቱ ከሚኖሩት ከነዓናውያን ጋራ ዐብረው ኖሩ፤ ይሁን እንጂ በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩት ለእነርሱ የጕልበት ሥራ ተገድደው ይሠሩ ነበር።
አሞራውያንም በሔሬስ ተራራ፣ በኤሎንና በሻዓልቢም ኑሯቸውን ቀጠሉ፤ ይሁን እንጂ የዮሴፍ ወገን በበረታ ጊዜ ተገድደው የጕልበት ሥራ ከመሥራት አላመለጡም።
በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም። የዳን ነገድም በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስተ ድርሻውን ገና ስላልወሰደ፣ የሚሰፍርበትን የራሱን ርስት ይፈልግ ነበር።