“ሰው ከጭቈና ብዛት የተነሣ ይጮኻል፤ ከኀያሉም ክንድ ሥር ለመውጣት ለርዳታ ይጣራል።
ካህናትን ከክህነታቸው ያዋርዳል፤ ለዘመናት የተደላደሉትንም ይገለብጣል።
ድኾችን በመጨቈን ባዶ አስቀርቷቸዋልና፣ ያልሠራውንም ቤት ነጥቋል።
የሟቾች ጣር ጩኸት ከከተማዋ ይሰማል፤ የቈሰሉት ሰዎች ነፍስ ለርዳታ ይጮኻል፤ እግዚአብሔር ግን ተጠያቂዎቹን ዝም ብሏል።
የድኾች ልቅሶ ወደ እርሱ እንዲደርስ ሰበብ ሆኑ፤ የመከረኞችን ጩኸት ሰማ።
ክፋትህ የሚጐዳው እንደ አንተ ያለውን ሰው ብቻ ነው፤ ጽድቅህም የሚጠቅመው የሰውን ልጆች ብቻ ነው።
እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ድምፅህስ እንደ እርሱ ድምፅ ሊያንጐደጕድ ይችላልን?
የክፉውንና የበደለኛውን ክንድ ስበር፤ የእጁንም ስጠው፤ ምንም እስከማይገኝ ድረስ።
እግዚአብሔር፣ “ስለ ችግረኞች መከራ፣ ስለ ድኾችም ጩኸት፣ አሁን እነሣለሁ፤ በናፈቁትም ሰላም አኖራቸዋለሁ” ይላል።
አምላክ ሆይ፤ አንተ ብርታቴ ነህና፣ ለምን ተውኸኝ? ጠላትስ እያስጨነቀኝ፣ ለምን በሐዘን እመላለሳለሁ?
ከብዙ ዓመት በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በባርነት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሣ ይጮኹ ነበር፤ ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያሰሙትም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ደረሰ።
ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በርግጥ እሰማለሁ።
ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ።
አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብጻውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ።
እንደ ገና ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤ የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።
ከልባቸው ወደ እኔ አይጮኹም፤ ነገር ግን በዐልጋቸው ላይ ሆነው ያለቅሳሉ። ስለ እህልና ስለ አዲስ የወይን ጠጅ ይሰበሰባሉ፤ ነገር ግን ከእኔ ዘወር ብለዋል።
የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጕጕት ይጠባበቀዋልና። አለዚያ ወደ እግዚአብሔር ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል።