“እርሱ ግን ራሱን ችሎ ብቻውን የሚኖር ነው፤ የሚቋቋመውስ ማን ነው? እርሱ የፈቀደውን ያደርጋል።
“ይህን ሁሉ ግን በልብህ ሸሸግህ፤ ነገሩ በሐሳብህ እንደ ነበር ዐውቃለሁ፤
እኔ በደለኛ እንዳልሆንሁ፣ ከእጅህም ሊያስጥለኝ ማንም እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።
“እርሱ ተከታትሎ መጥቶ በግዞት ቢያስቀምጥህ፣ የፍርድ ሸንጎም ቢሰበስብ፣ ማን ሊከለክለው ይችላል?
እርሱ ያፈረሰውን መልሶ የሚገነባ የለም፣ እርሱ ያሰረውን የሚፈታ አይገኝም።
ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከዕለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ።
በእኔ ላይ የወሰነውን ይፈጽማል፤ ይህን የመሰለ ዕቅድም ገና ብዙ አለው።
እርሱ ዝም ቢል፣ ማን ሊፈርድ ይችላል? ፊቱንስ ቢሰውር፣ ማን ሊያየው ይችላል? እርሱ ከሰውም፣ ከሕዝብም በላይ ነው፤
አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል።
በሰማይና በምድር፣ በባሕርና በጥልቅ ሁሉ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ደስ ያሠኘውን ሁሉ ያደርጋል።
በሰው ልብ ብዙ ሐሳብ አለ፤ የሚፈጸመው ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው።
የተጣመመው ሊቃና አይችልም፤ የሌለም ነገር ሊቈጠር አይችልም።
አምላክ ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ይህን አደረገ።
የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ፤ ‘ምክሬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሠኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።
ከምሥራቅ ነጣቂ አሞራ፣ ከሩቅ ምድር ዐላማዬን የሚፈጽም ሰው እጠራለሁ። የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤ ያቀድሁትን እፈጽማለሁ።
የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይ ኀይላት፣ በምድርም ሕዝቦች ላይ፣ የወደደውን ያደርጋል፤ እጁን መከልከል የሚችል የለም፤ “ምን ታደርጋለህ?” ብሎ የሚጠይቀውም የለም።
ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሠናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል።
በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም።