“የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምስጢር ልትለካ ትችላለህን? ወይስ ሁሉን ቻዩን አምላክ መርምረህ ትደርስበታለህን?
“እግዚአብሔር ከፍ ባለው ሰማይ የሚኖር አይደለምን? በሩቅ ከፍታ ያሉትን ከዋክብት ያያል!
እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው! የኀይሉንስ ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?”
“ስለ እግዚአብሔር ክንድ አስተምራችኋለሁ፤ የሁሉን ቻዩንም አምላክ ዕቅድ አልሸሽግም።
“ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰው ስለሚበልጥ፣ ትክክል እንዳልሆንህ እነግርሃለሁ።
የሰውን አቤቱታ እንደማይሰማ፣ ለምን ታማርርበታለህ?
ቀና ብለህ ወደ ሰማይ እይ፤ ከአንተ በላይ ከፍ ብለው ያሉትንም ደመናት ተመልከት።
እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአእምሯችን በላይ ታላቅ ነው! የዘመኑም ቍጥር ከመታወቅ ያልፋል።
ሁሉን ቻይ አምላክ ከአእምሯችን በላይ ነው፤ በኀይልና በፍርድ ታላቅ ነው፣ ጽድቁም ብዙ ነው፤ ማንንም አይጨቍንም።
የእግዚአብሔር ድምፅ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያንጐደጕዳል፤ እኛ የማናስተውለውንም ታላቅ ነገር ያደርጋል።
አንተ፣ ‘ያለ ዕውቀት ዕቅዴን የሚያደበዝዝ ይህ ማን ነው?’ አልኸኝ፤ በርግጥ ያልገባኝን ነገር፣ የማላውቀውንና ላስተውለው የማልችለውን ጕዳይ ተናገርሁ።
እርሱ፣ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮች፣ የማይቈጠሩም ታምራት ያደርጋል።
እንዲህ ያለው ዕውቀት ለእኔ ድንቅ ነው፤ ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው።
እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም።
መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፤ መሄጃህም በታላቅ ውሃ ውስጥ ነው፤ ዱካህ ግን አልታወቀም።
ወደ ሰማይ የወጣ፣ የወረደስ ማነው? ነፋስን በእጁ ሰብስቦ የያዘ ማነው? ውሆችንስ በመጐናጸፊያው የጠቀለለ ማነው? የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የወሰነ ማነው? ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል? የምታውቅ ከሆነ እስኪ ንገረኝ!
ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ አምላክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።
ጥበብ ምንም ይሁን ምን፣ እጅግ ጥልቅና ሩቅ ነው፤ ማንስ ሊደርስበት ይችላል?
አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።
“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።
የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!
እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።
“ያስተምረው ዘንድ፣ የጌታን ልብ ያወቀ ማን ነው?” እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ።