“እጅህ አበጀችኝ፤ ሠራችኝም፤ መልሰህ ደግሞ ታጠፋኛለህን?
የክፉዎችን ዕቅድ በደስታ እየተቀበልህ፣ እኔን ግን ስታስጨንቀኝ፣ የእጅህንም ሥራ ስታዋርድ ደስ ይልሃልን?
ሊከስሰኝ የሚችል አለ? ካለም፣ ዝም ብዬ ሞቴን እጠብቃለሁ።
ለሕያዋን ሁሉ ወደ ተመደበው ስፍራ፣ ወደ ሞት እንደምታወርደኝ ዐውቃለሁ።
በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፤ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል፤
ሁሉም አንድ ነው፤ ‘እርሱ ጻድቁንና ኀጥኡን ያጠፋል’ የምለውም ለዚህ ነው።
እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቁ፤ እርሱ ፈጠረን፤ እኛም የርሱ ነን፤ እኛ ሕዝቡ የማሰማሪያው በጎች ነን።
እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።
እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለውን ዐላማ ይፈጽማል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ለዘላለም ነው። የእጅህንም ሥራ ቸል አትበል።
እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤ በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣
ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ።
እርሱ የሁሉን ልብ የሠራ፣ የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያስተውል ነው።
በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።”