የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር።
እነዚህ በሠረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክሕታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው።
ነፍሴ በእግዚአብሔር ተመካች፤ ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ።
ኑና ከእኔ ጋራ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።
ዘወትር በእግዚአብሔር እንመካለን፤ ስምህንም ለዘላለም እንወድሳለን። ሴላ
አሁን ግን እነሆ ትተኸናል፤ አሳፍረኸናልም፤ ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ።
“ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ።
ፍትሕን የምትወድድ፣ ኀያል ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትክክለኝነትን መሠረትህ፤ ፍትሕንና ቅንነትንም፣ ለያዕቆብ አደረግህ።
በኢትዮጵያ ተስፋ ያደረጉ፣ በግብጽ የተመኩ ይፈራሉ፤ ይዋረዳሉም።
ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል። አንተ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእስራኤል ቅዱስ ሞገስ ታገኛለህ።
ነገር ግን የእስራኤል ዘር ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ሞገስንም ያገኛሉ።
“እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን ስለምወድድ፣ ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ፤ በታማኝነቴም የሚገባቸውን እሰጣቸዋለሁ፤ ከእነርሱም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
የድኾችንና የችግረኞችን ፍትሕ አላጓደለም፤ ስለዚህም ሁሉ መልካም ሆነለት። እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር።
በእውነት፣ በቅንነትና በጽድቅ፣ ‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለህ ብትምል፣ አሕዛብ በርሱ ይባረካሉ፤ በርሱም ይከበራሉ።”
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።
“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።”
እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።
ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።
እንግዲህ፣ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ “የሚመካ በጌታ ይመካ።”
ነገር ግን፣ “የሚመካ በጌታ ይመካ”፤
በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቷልና።
ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር፣ ሌላ ትምክሕት ፈጽሞ ከእኔ ይራቅ።
እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።