በሐዘኔ የምታጽናናኝ ሆይ፤ ልቤ በውስጤ ዝላለች።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈጥነህ መልስልኝ፤ መንፈሴ ደከመች፤ ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልሆን፣ ፊትህን ከእኔ አትሰውር።
ስለዚህ፣ “ከእኔ ራቁ፤ አምርሬ ላልቅስበት፣ ስለ ሕዝቤ ጥፋት፣ ልታጽናኑኝ አትሞክሩ” አልሁ።
ስለ ነቢያት፣ ልቤ በውስጤ ተሰብሯል፤ ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣ እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።
ወይ አበሳዬ! ወይ አበሳዬ! ሥቃይ በሥቃይ ላይ ሆነብኝ፤ አወይ፣ የልቤ ጭንቀት! ልቤ ክፉኛ ይመታል፤ ዝም ማለት አልችልም፤ የመለከትን ድምፅ፣ የጦርነትንም ውካታ ሰምቻለሁና።
ስለ እነርሱ ወሬ ደርሶናል፤ ክንዶቻችንም ዝለዋል፤ ጭንቀት ይዞናል፤ እንደምታምጥም ሴት ሆነናል።
ስለ ታረዱት ወገኖቼ፣ ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፣ ምነው፣ ራሴ የውሃ ምንጭ በሆነ! ምነው ዐይኖቼ የእንባ መጕረፊያ በሆኑልኝ!
ከዚህ የተነሣ ልባችን ደከመ፤ ከእነዚህ የተነሣም ዐይናችን ፈዘዘ፤
እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤ እግሬም ተብረከረከ፤ ሆኖም በሚወርረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣ የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።