የሕዝቤን ቍስል ብርቱ እንዳይደለ በመቍጠር፣ የተሟላ ፈውስ ሳይኖር እንዲሁ ያክማሉ፤ ሰላም ሳይኖር፣ “ሰላም፣ ሰላም” ይላሉ።
ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው።
ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ልዝመት ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።
እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ! ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ዘለቄታ ያለው እውነተኛ ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይላል ይሏቸዋል” አልሁ።
እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።
የሕዝቤን ቍስል እንደ ቀላል ቈጠሩ፣ እንዲፈወስም ተገቢውን እንክብካቤ አላደረጉለትም፤ ሰላምም ሳይኖር፣ ‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ።
ሰላምን ተስፋ አደረግን፤ መልካም ነገር ግን አልመጣም፤ የፈውስ ጊዜን ተመኘን፤ ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነብን።
የነቢያቶችሽ ራእይ፣ ሐሰትና ከንቱ ነው፤ ምርኮኛነትሽን ለማስቀረት፣ ኀጢአትሽን አይገልጡም። የሚሰጡሽም የትንቢት ቃል፣ የሚያሳስትና ከመንገድ የሚያወጣ ነው።
እኔ ያላሳዘንሁትን ጻድቅ በውሸት ስላሳዘናችሁ፣ ኀጢአተኛም ከክፉ መንገዱ ተመልሶ ሕይወቱን እንዳያድን በኀጢአቱ ስላበረታታችሁት፣
ሐሰተኛና አታላይ ሰው መጥቶ፣ ‘ስለ ብዙ የወይን ጠጅና ስለሚያሰክር መጠጥ ትንቢት እነግራችኋለሁ’ ቢል፣ ለዚህ ሕዝብ ተቀባይነት ያለው ነቢይ ይሆናል።
ሰዎች፣ “ሰላምና ደኅንነት ነው” ሲሉ፣ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት እንዲሁ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም።