ባቢሎን ሆይ፤ ወጥመድ ዘርግቼልሻለሁ፤ አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ እግዚአብሔርን ተገዳድረሻልና፣ ተገኘሽ፤ ተያዝሽም።
እጁን በእግዚአብሔር ላይ አንሥቷልና፤ ሁሉን ቻዩን አምላክም ደፍሯል፤
“ከሁሉን ቻይ አምላክ ጋራ ተከራክሮ የሚረታው አለን? እግዚአብሔርን የሚወቅሥ እርሱ መልስ ይስጥ!”
እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ድምፅህስ እንደ እርሱ ድምፅ ሊያንጐደጕድ ይችላልን?
ጥበቡ ጥልቅ፣ ኀይሉም ታላቅ ነውና፤ እርሱን ተቃውሞ ያለ አንዳች ጕዳት የሄደ ማን ነው?
ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው።
ደግሞም የራሱን ጊዜ የሚያውቅ ሰው የለም፤ ዓሦች በክፉ መረብ እንደሚያዙ፣ ወይም ወፎች በወጥመድ እንደሚጠመዱ፣ ሰዎችም ሳያስቡት በሚመጣባቸው፣ በክፉ ጊዜ ይጠመዳሉ።
ዓለምን ስለ ክፋቷ፣ ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችን እብሪት እሽራለሁ፤ የጨካኞችንም ጕራ አዋርዳለሁ።
“ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ ከሠሪው ጋራ ክርክር ለሚገጥም ወዮለት! ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣ ‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን? የምትሠራውስ ሥራ፣ ‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?
የሞዓብ ሕዝብ ሆይ፤ ሽብርና ጕድጓድ፣ ወጥመድም ይጠብቅሃል፤” ይላል እግዚአብሔር።
“ከሽብር የሚሸሽ ሁሉ፣ ጕድጓድ ውስጥ ይገባል፤ ከጕድጓዱም የሚወጣ፣ በወጥመድ ይያዛል፤ በሞዓብ ላይ፣ የቅጣቱን ዓመት አመጣለሁና፣” ይላል እግዚአብሔር።
ባለሥልጣኖቿንና ጥበበኞቿን፣ ገዦቿንና መኳንንቷን፣ ጦረኞቿንም አሰክራለሁ፤ ለዘላለም ይተኛሉ፤ አይነቁምም፤” ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ።
ባቢሎን በድንገት ወድቃ ትሰበራለች፤ ዋይ በሉላት! ምናልባት ልትፈወስ ስለምትችል፣ ለቍስሏ የሚቀባ መድኀኒት ፈልጉላት።
እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል።