እኔ ግን ዔሳውን አራቍተዋለሁ፤ መደበቅም እንዳይችል፣ መሸሸጊያ ስፍራዎቹን እገልጣለሁ፤ ልጆቹ፣ ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ ይጠፋሉ፤ እርሱም ራሱ አይኖርም።
እግዚአብሔር ፍትሕን ይወድዳልና፣ ታማኞቹንም አይጥልም። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል።
እነሆ፤ ሲመሽ ድንገተኛ ሽብር ሆነ! ከመንጋቱ በፊት ግን አንዳቸውም አልተገኙም። የዘረፉን ዕድል ፈንታ፣ የበዘበዙን ዕጣ ይህ ሆነ።
በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣ በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣ በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።
“ኀፍረትሽ እንዲገለጥ፣ ልብስሽን ፊትሽ ድረስ እገልባለሁ፤
እኔ እንዳላየው፣ በስውር ቦታ ሊሸሸግ የሚችል አለን?” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን” ይላል እግዚአብሔር።
የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ቅጣትሽ ያበቃል፤ እርሱም የስደትሽን ዘመን አያራዝምም፤ ነገር ግን አንቺ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፤ ኀጢአትሽን ይቀጣል፤ ክፋትሽንም ይፋ ያወጣል።
በቀርሜሎስ ጫፍ ላይ ቢሸሸጉም፣ ዐድኜ፣ ፈልጌ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ እይዛቸዋለሁም። በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከእኔ ቢሸሸጉም፣ በዚያ እባቡ እንዲነድፋቸው አዝዘዋለሁ።
ዔሳው ግን እንዴት ተዘረፈ? የሸሸገውስ ሀብት ምንኛ ተመዘበረ!
“ቴማን ሆይ፤ ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ፤ በዔሳውም ተራሮች ያለ ሁሉ፣ ተገድሎ ይጠፋል።
ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።