“ራሱን በባርነት ለእናንተ የሸጠውን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ በየሰባት ዓመቱ ነጻ ትለቅቃላችሁ፤ ስድስት ዓመት ከተገዛላችሁ በኋላ ነጻ ታወጡታላችሁ።” አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሯቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም።
በሚስቱ በኤልዛቤል ተገፋፍቶ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራሱን የሸጠ እንደ አክዓብ ያለ ሰው ከቶ አልነበረም።
ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ ይልቁንም እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አዛዦቹ፣ ሻምበሎቹ፣ የፈረሰኞችና የሠረገለኞች አዛዦቹ ነበሩ።
አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች፣ ባሪያዎቻችሁ ልታደርጓቸው ትፈልጋላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ ኀጢአት ሠርታችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አልበደላችሁምን?
እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሣለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።
ብዙ ዘመን ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህ አማካይነት በመንፈስህ አስጠነቀቅሃቸው። ነገር ግን አላደመጡህም፤ ከዚህም የተነሣ ጎረቤቶቻቸው ለሆኑ አሕዛብ አሳልፈህ ሰጠሃቸው።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እናታችሁን የፈታሁበት የፍች ወረቀት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥኋችሁ ለየትኛው አበዳሪዬ ነው? እነሆ፤ ስለ ኀጢአታችሁ ተሸጣችኋል፤ ስለ መተላለፋችሁም እናታችሁ ተፈትታለች።
“እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን?
የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ “ታዘዙኝ” በማለት ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው።
“የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ከክፉ ነገር በቀር በፊቴ አንዳች በጎ ነገር አልሠሩም፤ በርግጥም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ አስቈጡኝ፤ ይላል እግዚአብሔር።
አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ወደ እናንተ ላክሁ፤ እነርሱም፣ “እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ምግባራችሁን አስተካክሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖሩ ዘንድ ሌሎቹን አማልክት ለማገልገል አትከተሉ” አልኋችሁ። እናንተ ግን ጆሯችሁን ወደ እኔ አላዘነበላችሁም፤ አልሰማችሁኝምም።
“የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጥላቸው፤
“ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብጽ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።
ዐምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ ድኻውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና።
ድኻውን በብር፣ ችግረኛውንም በጥንድ ጫማ እንገዛለን፤ ግርዱን እንኳ በስንዴ ዋጋ እንሸጣለን።
እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል?
በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት አድርግ።
ወገንህ የሆነ ዕብራዊ ወንድን ወይም ሴትን ገዝተህ ስድስት ዓመት ካገለገለህ፣ በሰባተኛው ዓመት በነጻ ይሂድ።
“ዕዳ የሚሠረዝበት ሰባተኛው ዓመት ተቃርቧል” የሚል ምናምንቴ ሐሳብ ዐድሮብህ፣ በድኻ ወንድምህ ላይ እንዳትጨክንና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር፣ እርሱም በአንተ ላይ ወደ እግዚአብሔር ጮኾ በደለኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!