ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።’
ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባርረህ እርሷን ተከልሃት።
ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤ ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣ የእጆቼ ሥራ፣ እኔ የተከልኋቸው ቍጥቋጦች ናቸው።
ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ ነገር ግን፣ “ደስታዬ በርሷ” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፣ “ባለባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባለባል ትሆናለች።
ጕልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣ ልጆችሽ እንዲሁ ያገቡሻል፤ ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣ አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።
በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤ በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤ የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።
በሌላም ጊዜ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት አንጸውና እተክለው ዘንድ ተናግሬ፣
ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
ከዚያም በዙሪያችሁ የነበሩ የቀሩት አሕዛብ ፈርሶ የነበረውን መልሼ የሠራሁ፣ ጠፍ የነበረውን ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እኔም አደርገዋለሁ።’
እኔ ለእስራኤል እንደ ጠል እሆናለሁ፤ እንደ ውብ አበባ ያብባል፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም፣ ሥር ይሰድዳል፤
እስራኤልን በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤ ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛ አይነቀሉም፤” ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።
የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
እግዚአብሔር እናንተን በማበልጸግና ቍጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሠኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።
ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉና በወገብህ ፍሬ፣ በእንስሳትህ ግልገሎችና በምድርህ ሰብል እጅግ ያበለጽግሃል። በአባቶችህ ደስ እንደ ተሠኘ ሁሉ፣ እግዚአብሔር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና።