ነገር ግን፣ ‘እስራኤልን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ይላሉ፤ ከዚያ በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።”
በዚያ ቀን፣ ጌታ እጁን ዘርግቶ እንደ ገና የተረፈውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦር፣ ከግብጽ፣ ከጳትሮስ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኤላም፣ ከባቢሎን፣ ከሐማትና ከባሕር ጠረፍ ምድር ይሰበስባል።
እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤ እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤ በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል። መጻተኞች ዐብረዋቸው ይኖራሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋራ ይተባበራሉ።
“ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤
“ነገር ግን፣ ‘እስራኤላውያንን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ይላሉ፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁና።
“የመንጋዬንም ቅሬታ ካባረርሁባቸው አገሮች ሁሉ እኔ ራሴ ሰብስቤ፣ ወደ መሰማሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ይበዛሉም።
እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”
“ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤ እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘አንተን ከሩቅ አገር፣ ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤ ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም አይኖርም።
እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”
እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዕውሮችና ዐንካሶች፣ ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤ ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።
‘በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ ያለ ሥጋትም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።
ከዚህ ክፉ ሕዝብ የተረፉት ሁሉ፣ ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፤ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤልን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች መካከል በምሰበስብበት ጊዜ፣ አሕዛብ እያዩ ቅድስናዬን በመካከላቸው እገልጣለሁ፤ ከዚያም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ፤ ይህም ለባሪያዬ ለያዕቆብ የሰጠሁት ነው።
ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።
“ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ።
እነርሱም፣ “ጠፍ የነበረው ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት መሰለ፤ የተደመሰሱ፣ የፈራረሱና ባድማ የሆኑት ከተሞች አሁን መኖሪያና ምሽግ ሆነዋል” ይላሉ።
አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል።
በአሕዛብ መካከል እንዲሰደዱ ባደርግም፣ አንድም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
“እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ።
“ከግብጽ እንደ ወጣህበት ዘመን ሁሉ፣ ታምራቴን አሳያቸዋለሁ።”
በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።