እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።
የእስራኤል አምላክ ተናገረ፤ የእስራኤልም ዐለት እንዲህ አለኝ፤ ‘ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔርም የሚያስተዳድር፣
እንዲሁም ንጹሕ ደም ስላፈሰሰ ነው። ኢየሩሳሌምም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ፤ እግዚአብሔር ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።
መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰድደሃል፤ የድኻ አደጎችንም ክንድ ሰብረሃል።
አባት የሌለው ልጅ ከዕቅፍ ተነጥቋል፤ የድኻውም ልጅ በዕዳ ተይዟል።
እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው።
ወገን የሌለውንና ድኻውን ታደጉ፤ ከግፈኛውም እጅ አስጥሏቸው።
በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤ በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ።
መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤ የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ።
“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብጽ መጻተኛ ነበራችሁና።
“ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ።
የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ፤ አባት የሌላቸውንም ልጆች መሬት አትግፋ፤
ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈስሱ እጆች፣
ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።
“እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን?
ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን?
እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤
የዳዊት ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ካደረጋችሁት ክፋት የተነሣ፣ ቍጣዬ እንዳይቀጣጠል፣ ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል እንዳይነድድ፣ በየማለዳው ፍትሕን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ሰው፣ ከጨቋኙ እጅ አድኑት።
“የአንተ ዐይንና ልብ ያረፉት ግን፣ አጭበርብሮ ጥቅምን በማግኘት፣ የንጹሑን ደም በማፍሰስ፣ ጭቈናንና ግፍን በመሥራት ላይ ብቻ ነው።”
ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሯልና ሊገደል አይገባውም” አሉ።
ወፍረዋል፤ ሠብተዋልም። ክፋታቸው ገደብ የለውም፤ ወላጅ የሌላቸው ፍትሕ እንዲያገኙ አልቆሙላቸውም፤ ለድኾችም መብት አልተከራከሩም።
ነገር ግን ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ መልካም እንዲሆንላችሁም፣ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ አዘዝኋቸው።
የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር።
ሰው ፍትሕ ሲጓደልበት፣ ጌታ እንዲህ ዐይነቱን ነገር አያይምን?
ድኻውንና ችግረኛውን ቢጨቍን፣ በጕልበት ቢቀማ፣ በመያዣነት የወሰደውን ባይመልስ፣ ወደ ጣዖታት ቢመለከት፣ አስጸያፊ ተግባራትን ቢፈጽም፣
ማንንም አይጨቍንም፤ ነገር ግን በመያዣ የወሰደውን እንኳ ለተበዳሪው ይመልሳል፤ ለተራበ የራሱን እንጀራ፣ ለተራቈተም ልብስ ይሰጣል እንጂ፣ በጕልበት አይቀማም።
አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ፤ መጻተኞች ተጨቈኑ፤ ድኻ አደጎችና መበለቶች ተንገላቱ።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ግብጽ ባድማ፣ ኤዶምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ፣ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ፈጽመዋልና።
“ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታድላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በጽድቅ ፍረድ።
ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤ በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር፣ ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።
ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።
መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
“ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤
እርሱ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች ይፈርዳል፤ መጻተኛውንም ምግብና ልብስ በመስጠት ይወድዳል።
ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ።
አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፣ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፣ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ።
“በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።