አንበሶች በርሱ ላይ አገሡ፤ በኀይለኛ ድምፅም ጮኹበት። ምድሩን ባድማ አድርገውበታል፤ ከተሞቹ ተቃጥለዋል፤ ወናም ሆነዋል።
አንበሳ ያገሣል፤ ቍጡውም አንበሳ ይጮኻል፤ የደቦል አንበሳው ጥርስ ግን ተሰብሯል።
ነፍሴ በአንበሶች ተከብባለች፤ በሚዘነጣጥሉ አራዊት መካከል ወድቄአለሁ፤ እነዚህም፣ ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፣ ምላሳቸውም የተሳለ ሰይፍ የሆኑ ሰዎች ናቸው።
አገራችሁ ባድማ፣ ከተሞቻችሁ በእሳት የተቃጠሉ ይሆናሉ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ መሬታችሁ በባዕድ ይነጠቃል፤ ጠፍም ይሆናል።
እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድርን ባድማ ያደርጋታል፤ ፈጽሞ ያጠፋታል፤ የፍርስራሽ ክምር ያደርጋታል፤ ነዋሪዎቿንም ይበትናል።
ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤ ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤ ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ታላላቅ ቤቶች ወና ይቀራሉ፣ የሚያማምሩም ቤቶች ኗሪ ያጣሉ።
እኔም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” አልሁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፤ “ከተሞች እስኪፈራርሱና የሚኖሩባቸው እስኪያጡ፣ ቤቶችም ወና እስኪሆኑና ምድርም ፈጽሞ ባድማ እስክትሆን ድረስ፤
መርዶ ስሙ! እነሆ፤ ከሰሜን ምድር፣ ታላቅ ሽብር እየመጣ ነው፤ የይሁዳን ከተሞች ባድማ፣ የቀበሮዎችም መናኸሪያ ያደርጋል።
“እንግዲህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገርባቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ “ ‘እግዚአብሔር ከላይ ይጮኻል፤ ከቅዱስ ማደሪያው ነጐድጓዳማ ድምፁን ያሰማል፤ በራሱ ምድር ላይ እጅግ ይጮኻል፤ እንደ ወይን ጨማቂዎች፣ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይም ያስገመግማል፤
የሰሜንን ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ሰዎች የሚጸየፏቸውና የሚሣለቁባቸው፣ የዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ፤
ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይህችም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ በእግዚአብሔር ስም ለምን ትንቢት ትናገራለህ?” ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተሰብስበው ኤርምያስን ከበቡት።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህችን ስፍራ፣ “ሰውና እንስሳት የማይኖሩባት ባድማ ናት” ትላላችሁ፤ ነገር ግን ሰውም ሆነ እንስሳ ባልነበሩባቸውና ባድማ በሆኑት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች፣ እንደ ገና ድምፅ ይሰማል፤
እነሆ፤ አዝዛቸዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ወደዚህችም ከተማ እንደ ገና እመልሳቸዋለሁ። እነርሱም ይወጓታል፤ ይይዟታል፤ በእሳትም ያቃጥሏታል። የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይኖርባቸው፣ ባድማ አደርጋቸዋለሁ።’ ”
አንበሳ ከደኑ ወጥቷል፤ ሕዝብንም የሚያጠፋ ተሰማርቷል፤ ምድርሽን ባዶ ሊያደርግ፣ ከስፍራው ወጥቷል። ከተሞችሽ ፈራርሰው ይወድቃሉ፤ ያለ ነዋሪም ይቀራሉ።
እግዚአብሔር ክፉ አድራጎታችሁንና አስጸያፊ ተግባራችሁን ሊታገሥ ባለመቻሉ፣ ዛሬ እንደ ሆነው ምድራችሁ የርግማን ምልክትና ሰው የማይኖርበት ባዶ ምድረ በዳ ሆኗል።
ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰባብራቸዋል፣ የምድረ በዳ ተኵላም ይቦጫጭቃቸዋል፤ ብቅ የሚለውን ሰው ሁሉ ለመገነጣጠል፣ ነብር በከተሞቻቸው ዙሪያ ያደባል፤ ዐመፃቸው ታላቅ፣ ክሕደታቸው ብዙ ነውና።
“እስራኤል አንበሶች ያሳደዱት፣ የተበተነ መንጋ ነው፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ፣ ቦጫጭቆ በላው፤ በኋላም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ ዐጥንቱን ቈረጣጠመው።”
ሕዝቦቿ ሁሉ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤ እንደ አንበሳ ግልገልም ያጕረመርማሉ።
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተጠንቀቂ፤ አለዚያ ከአንቺ ዘወር እላለሁ፤ ማንም ሊኖርባት እስከማይችል ድረስ፣ ምድርሽን ባዶ አደርጋለሁ።”
ስለ ተራሮች አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይ እላለሁ፤ በምድረ በዳ ስላሉትም መሰማሪያዎች ዐዝናለሁ። ሰው የማያልፍባቸው ባድማ ሆነዋል፤ የከብቶች ጩኸት አይሰማም፤ የሰማይ ወፎች ሸሽተዋል፤ የዱር አራዊትም ጠፍተዋል።
“ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣ የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤ የይሁዳንም ከተሞች፣ ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከየአቅጣጫው ከብበው በመውጋት ስላጠቋችሁ፣ ለቀሩት ሕዝቦች ሁሉ ርስት ሆናችሁ፤ ለሕዝብም መሣቂያና መሣለቂያ ሆናችሁ።
“በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ መካከል፤ በአጠገብሽም በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሣለቂያ አደርግሻለሁ።
እግዚአብሔርን ይከተላሉ፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ እርሱ ሲያገሣ፣ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ።
እኔ ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፣ ለይሁዳም እንደ ደቦል አንበሳ እሆናለሁና፤ ሰባብሬና አድቅቄአቸው እሄዳለሁ፤ ነጥቄ እወስዳቸዋለሁ፤ ማንም ሊያድናቸው አይችልም።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እረኛ ከአንበሳ መንጋጋ፣ ሁለት የእግር ዐጥንት ወይም የጆሮ ቍራጭ እንደሚያድን፣ እንዲሁም በሰማርያ በዐልጋቸው ጫፍ ላይ፣ በደማስቆም በምንጣፋቸው ላይ የተቀመጡ፣ እስራኤላውያን ይድናሉ።”
አንበሳ የሚበላውን ሳያገኝ፣ በጫካ ውስጥ ይጮኻልን? ምንም ነገርስ ሳይዝ፣ በዋሻው ውስጥ ያገሣልን?
አንበሳ አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?
አሁን ታዲያ የአንበሶቹ ዋሻ፣ ደቦሎቻቸውን ያበሉበት ወንዱና ሴቷ አንበሳ የሄዱበት፣ ግልገሎችም ሳይፈሩ የተሰማሩበት ቦታ ወዴት ነው?
በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም።” መላዪቱ ምድር፣ በቅናቱ ትበላለች፤ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ፣ ድንገተኛ ፍጻሜ ያመጣባቸዋልና።
እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፣ የከሊታውያን ሰዎች ሆይ፤ ወዮላችሁ! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፤ በአንቺ ላይ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ “ፍጹም አጠፋሻለሁ፤ ከነዋሪዎችሽም የሚተርፍ የለም።”
“ሕዝቦችን አጥፍቻለሁ፤ ምሽጋቸው ተደምስሷል፤ ማንም እንዳያልፍባቸው፣ መንገዳቸውን ባድማ አደረግሁ፤ ከተሞቻቸው ተደምስሰዋል፤ አንድም ሰው የለም፤ ነዋሪም ከቶ አይገኝባቸውም።
የእረኞችን ዋይታ ስሙ፤ ክብራቸው ተገፍፏልና፤ የአንበሶችን ጩኸት ስሙ፤ ጥቅጥቅ ያለው የዮርዳኖስ ደን ወድሟል!
ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋራ ወደ ተምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት።