“አሁንም እንግዲህ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ጥፋትን እያዘጋጀሁላችሁ ነው፤ ክፋትንም እየጠነሰስሁላችሁ ነው። ስለዚህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁን አቅኑ።” ’
ኑ እንውረድ፤ እርስ በርሳቸውም እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደበላልቀው።”
“ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል።”
ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።
“ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የነደደው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና።”
የሶርያም ንጉሥ፣ “በል እንግዲያው አሁኑኑ ሂድ፤ እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እጽፋለሁ” አለው፤ ስለዚህ ንዕማን ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺሕ ሰቅል ወርቅና ዐሥር ሙሉ ልብስ ይዞ ሄደ።
እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፣ መረጋገጫም ይሆናል።
ጻድቅ ይሞታል፤ ይህን ግን ማንም ልብ አይልም፤ ለእግዚአብሔር ያደሩ ሰዎች ይወሰዳሉ፤ ጻድቃን ከክፉ ይድኑ ዘንድ፣ መወሰዳቸውን፣ ማንም አያስተውልም።
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሊያመልጡት የማይችሉትን ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ወደ እኔ ቢጮኹም አልሰማቸውም።
እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት ነበርሁ፤ እነርሱም፣ “ዛፉን ከፍሬው ጋራ እንቍረጥ፤ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው፤ ከእንግዲህም ወዲያ ስሙ አይታሰብ” ብለው እንዳደሙብኝ ዐላወቅሁም ነበር።
እነርሱም፣ “ሕግ ከካህናት፣ ምክር ከጠቢባን፣ ቃልም ከነቢያት ስለማይታጣ ኑና በኤርምያስ ላይ እንማከር፤ ኑ፤ በአንደበታችን እናጥቃው፣ እርሱ የሚናገረውንም ሁሉ አንስማ” አሉ።
“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ዐንገታቸውን በማደንደን ቃሌን ስላልሰሙ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ ባሉ መንደሮች ሁሉ ላይ ላደርስ ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ አመጣለሁ።’ ”
እንዲህም በል፤ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚዘገንን ክፉ ነገር እነሆ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ፤
ስለዚህ ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩትም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፤
እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እንግዲህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣት ምድር ለዘላለም ትቀመጣላችሁ።
አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል።
ምናልባትም ሰምተው እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስላደረጉት ክፋት ላመጣባቸው ያሰብሁትን ቅጣት እተዋለሁ።
“ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣ እርሷም ሄዳ ሌላ ሰው ብታገባ፣ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ምድሪቱስ ፈጽማ አትረክስምን? አንቺ ግን ከብዙ ወዳጆችሽ ጋራ አመንዝረሻል፤ ታዲያ አሁን ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽን?” ይላል እግዚአብሔር።
“እናንተ ከዳተኞች ልጆች ተመለሱ፤ ከዳተኝነታችሁን እፈውሳለሁ። “አንተ እግዚአብሔር አምላካችን ነህና፤ አዎን፤ ወደ አንተ እንመጣለን።
አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ወደ እናንተ ላክሁ፤ እነርሱም፣ “እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ምግባራችሁን አስተካክሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖሩ ዘንድ ሌሎቹን አማልክት ለማገልገል አትከተሉ” አልኋችሁ። እናንተ ግን ጆሯችሁን ወደ እኔ አላዘነበላችሁም፤ አልሰማችሁኝምም።
ምናልባትም የይሁዳ ሕዝብ ላመጣባቸው ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ ሲሰሙ፣ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ክፋታቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”
እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣና መቅሠፍት ታላቅ ስለ ሆነ፣ ምናልባት ልመናቸውን በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”
“እስራኤል ሆይ፤ ብትመለስ፣ ወደ እኔ ብትመለስ” ይላል እግዚአብሔር፤ “አስጸያፊ ነገሮችህን ከፊቴ ብታስወግድ፣ ባትናወጥ ብትቆምም፣
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እንድትድኚ ከልብሽ ክፋት ታጠቢ፤ እስከ መቼ ክፉ ሐሳብ በውስጥሽ ይኖራል?
ምድርን ተመለከትሁ፤ እነሆ ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች፤ ሰማያትንም አየሁ፣ ብርሃናቸው ጠፍቷል።
ወደ ጽዮን ለመግባት ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ ቶሎ ሸሽታችሁ አምልጡ፤ ከሰሜን መቅሠፍትን፣ ታላቅ ጥፋትን አመጣለሁና።”
“ፍላጾችን ሳሉ፤ ጋሻዎችን አዘጋጁ፤ የእግዚአብሔር ሐሳብ ባቢሎንን ለማጥፋት ስለ ሆነ፣ የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቷል፤ እግዚአብሔር ይበቀላል፤ ስለ ቤተ መቅደሱ ይበቀላል።
የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፤ እኔም በዚህ ስፍራ እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ።
እኔ ያላሳዘንሁትን ጻድቅ በውሸት ስላሳዘናችሁ፣ ኀጢአተኛም ከክፉ መንገዱ ተመልሶ ሕይወቱን እንዳያድን በኀጢአቱ ስላበረታታችሁት፣
በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን?
ነገር ግን ሰውም እንስሳም ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ ሰዎችም ሁሉ ክፉ መንገዳቸውንና የግፍ ሥራቸውን ይተዉ።
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ በዚያ ሕዝብ ላይ ጥፋት ላመጣ ዐቅጃለሁ፤ ከዚህም ለማምለጥ አትችሉም። ከእንግዲህ በትዕቢት አትመላለሱም፤ የመከራ ጊዜ ይሆናልና።
ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ።
እናንተ፣ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ።
እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ።