የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?
እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ።
እግዚአብሔርም ደስ የሚያሠኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ አላጠፋም።
በደብዳቤውም ላይ፣ “ኦርዮ ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ።
ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ።
እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤ እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ።
በራሱ የሚታመን ሞኝ ነው፤ በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም።
ከፀሓይ በታች በሁሉም ላይ የሚሆነው ክፋት ይህ ነው፤ የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው። በዚህም ላይ የሰዎች ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ በሕይወት እያሉም በልባቸው ውስጥ እብደት አለ፤ በመጨረሻም ወደ ሙታን ይወርዳሉ።
ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ? ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ? ራሳችሁ በሙሉ ታምሟል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኳል።
ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጕራችሁ ጤና የላችሁም፤ ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም።
የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሯቸውን ድፈን፤ ዐይኖቻቸውንም ክደን፤ ይህ ካልሆነማ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው በመመለስ ይፈወሳሉ።”
እናንተም ደግሞ ከአባቶቻችሁ የባሰ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ እያንዳንዳችሁ እኔን በመታዘዝ ፈንታ የልባችሁን ክፋት ምን ያህል በእልኸኝነት እንደምትከተሉ ተመልከቱ።
እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ።
የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’
ክፉ ሐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ማመንዘር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በሐሰት መመስከርና ስም ማጕደፍ ከልብ ይመነጫሉና።
ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው።
እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ።
ኀጢአት በትእዛዝ በኩል የተገኘውን ዕድል በመጠቀም አታለለኝ፤ በትእዛዝም ገደለኝ።
ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጐደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤
ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ።