እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትን፣ ካህናትን፣ ነቢያትን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሁሉ ጨምሮ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ።
ለሕዝብህ አበሳውን አሳየኸው፤ ናላ የሚያዞር የወይን ጠጅ እንድንጠጣም ሰጠኸን።
በእግዚአብሔር እጅ ጽዋ አለ፤ በሚገባ የተቀመመና ዐረፋ የሚወጣው የወይን ጠጅ ሞልቶበታል፤ ይህን ከውስጡ ወደ ውጭ ገለበጠው፤ የምድር ዐመፀኞችም አተላውን ሳይቀር ይጨልጡታል።
ነኹልሉ ተደነቁም፤ ተጨፈኑ፤ እስከ ወዲያኛውም ታውራችሁ ቅሩ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ።
አስጨናቂዎችሽ የራሳቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤ በወይን ጠጅ እንደሚሰከር ሁሉ፣ በገዛ ደማቸው ይሰክራሉ። ከዚያም የሰው ዘር ሁሉ፣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣ ታዳጊሽም የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።”
ከእግዚአብሔር እጅ፣ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ፣ ዝቃጩ እንኳ ሳይቀር፣ ሰዎችን የሚያንገደግደውን ዋንጫ የጨለጥሽ፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ተነሺ!
ስለዚህ አንቺ የተጐዳሽ፣ ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ ይህን ስሚ።
መንግሥታትን በቍጣዬ ረጋገጥሁ፤ በመዓቴም አሰከርኋቸው፤ ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስሁ።”
“እንዲህ በላቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ ይሞላል’፤ እነርሱም፣ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ እንደሚሞላ እኛ አናውቅምን?’ ቢሉህ፣
“አንተም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጠጡ፤ ስከሩ፤ አስታውኩም፤ ዳግመኛም ላትነሡ በመካከላችሁ በምሰድደው ሰይፍ ፊት ውደቁ።”
እነሆ፤ ስሜ የተጠራበትን ከተማ ማጥፋት እጀምራለሁ፤ ታዲያ ያለ ቅጣት ታመልጣላችሁን? ሳትቀጡ አትለቀቁም፤ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ሳትቀጡ አታመልጡም፤” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’
ባለሥልጣኖቿንና ጥበበኞቿን፣ ገዦቿንና መኳንንቷን፣ ጦረኞቿንም አሰክራለሁ፤ ለዘላለም ይተኛሉ፤ አይነቁምም፤” ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ።
ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ የወርቅ ጽዋ ነበረች፤ ምድርንም ሁሉ አሰከረች። ሕዝቦች ከወይን ጠጇ ጠጡ፤ ስለዚህ አሁን አብደዋል።
በክብር ፈንታ ዕፍረት ትሞላለህ፤ አሁን ደግሞ ተራው የአንተ ነውና ጠጣ፤ ኀፍረተ ሥጋህም ይገለጥ፤ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ያለው ጽዋ ይመለስብሃል፤ ክብርህንም ውርደት ይሸፍነዋል።